ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 16:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሳሙኤል እግዚአብሔር ያለውን ነገር አደረገ። ቤተ ልሔም እንደ ደረሰም፣ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፣ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት።

5. ሳሙኤልም፣ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው።

6. እዚያ በደረሱ ጊዜም፣ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞአል” ብሎ አሰበ።

7. እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።

8. ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንንም አልመረጠውም” አለው።

9. እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንም እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ።

10. እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው።

11. ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው።እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ።ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና” አለው።

12. ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው።

13. ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ።

14. የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 16