ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ።በዚያ ዘመን እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እስራኤላውያን በአቤንኤዘር፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ።

2. ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሰራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፣ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺህ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ።

3. ሰራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፣ ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፣ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ።

4. ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፣በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሰራዊት ጌታ የእግዚእብሔርን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።

5. የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፣ ምድሪቱ እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የደስታ ጩኸት አሰሙ።

6. ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ ጩኸት ሲሰሙ፣ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድ ነው?” ሲሉ ጠየቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤

7. ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቶአል፤ ወዮልን! እንዲህ ዐይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም።

8. ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤

9. ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ ወንድነታችሁም ይታይ፤ ያለዚያ ባሪያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፣ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባሪያ ያደርጓችኋል። ወንድነታችሁ ይታይ፤ ተዋጉ!”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 4