ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 8:14-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ከእርሻችሁ፣ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለ ሟሎቹ ይሰጣቸዋል።

15. ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለ ሟሎቹ ይሰጣቸዋል።

16. ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ለራሱ ያደርጋቸዋል።

17. ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተ ራሳችሁም ባሪያዎቹ ትሆናላችሁ።

18. ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ወዳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን እግዚአብሔር አይመልስላችሁም።”

19. ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እምቢ በማለት፤ እንዲህ አሉ፤ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን፤

20. እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፣ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።”

21. ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ በእግዚአብሔር ፊት ተናገረው።

22. እግዚአብሔርም፣ “አድምጣቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው።ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፣ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 8