ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 2:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳዊት የሚሞትበት ጊዜ እንደ ተቃረበም፣ ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤

2. “እነሆ፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው፤ እንግዲህ በርታ፤ ሰውም ሁን።

3. የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የምታደርገው ሁሉ እንዲከናወንልህ፣ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው በመንገዶቹ ተመላለስ፣ ሥርዐቶቹንና ትእዛዛቱን፣ ሕግጋቱንና ደንቦቹን ጠብቅ፤

4. እግዚአብሔርም፣ ‘ዘሮችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፣ እንዲሁም በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸው በታማኝነት በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው ከዘርህ አላሳጣህም’ ሲል የሰጠኝን ተስፋ ይፈጽምልኛል።

5. የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በእኔ ላይ ያደረገውን፣ እንዲሁም በእስራኤል ሰራዊት አዛዦች በኔር ልጅ በአበኔርና በዬቴሩ ልጅ በአሜሳይ ላይ የፈጸመውን አንተው ራስህ ታውቃለህ፤ ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደማቸውን አፍሶአል፤ በዚህም ደም ወገቡ ላይ የታጠቀውን ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገውን ጫማ በክሎአል።

6. መደረግ ያለበትን በጥበብህ አድርግ፤ ከነሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር እንዲወርድ አታድርግ።

7. “ከወንድምህ ከአቤሴሎም በሸሸሁ ጊዜ መልካም ነገር አድርገውልኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች ግን በጎ ነገር አድርግላቸው፤ ማእድህን ከሚካፈሉ ሰዎችም ጋር አብረው ይብሉ።

8. “ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ፣ ክፉኛ የረገመኝ የባሑሪም ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ እነሆ፤ ከአንተ ዘንድ ይገኛል፤ ሊቀበለኝ ወደ ዮርዳኖስ ሲወርድ፣ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም ምዬለታለሁ፤

9. አሁን ግን በደል እንደሌለበት ሰው አትተወው፤ ጥበበኛ ነህና መደረግ ያለበትን ታውቃለህ፤ ሽበቱን በደም ወደ መቃብር አውርድ።”

10. ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።

11. ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት ባጠቃላይ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።

12. ስለዚህ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ የጸና ሆነ።

13. በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ።

14. ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጒዳይ አለኝ” አላት።እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።

15. እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ።

16. አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት።እርሷም፣ “በል እሺ ተናገር” አለችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 2