ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 21:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ፣ “ዐፅመ ርስቴን አልለቅልህም” ስላለው፣ አክዓብ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ።

5. ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እርሱ ገብታ፣ “እስከዚህ የተበሳጨኸው፣ ምግብስ የማትበላው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው።

6. እርሱም፣ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፣ ‘የወይን ተክል ቦታህን ሽጥልኝ፤ ከፈለግህም በምትኩ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ’ አልሁት፤ እርሱ ግን፣ ‘የወይን ተክል ቦታዬን አልለቅልህም’ ስላለኝ ነው” አላት።

7. ሚስቱ ኤልዛቤልም፣ “አንተ አሁን የእስራኤል ንጉሥ ትባላለህ? በል ተነሥና እህል ቅመስ፤ ደስም ይበልህ፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እኔ እንድታገኝ አደርግሃለሁ” አለችው።

8. ስለዚህ በአክዓብ ስም ደብዳቤዎች ጻፈች፤ በገዛ ማኅተሙም አትማ በናቡቴ ከተማ አብረውት ለሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት ላከች።

9. በደብዳቤዎቹም ላይ እንዲህ ስትል ጻፈች፤“የአንድ ቀን ጾም ዐውጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀምጡት።

10. እንዲሁም ሁለት የሐሰት ምስክሮች ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና፣ ‘እግዚአብሔርንም ንጉሡንም ሰድቦአል’ ብለው ይመስክሩበት፤ ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉት።”

11. ስለዚህ በናቡቴ ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት በደብዳቤዎቹ ላይ እንደ ጻፈችላቸው አደረጉ።

12. የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀመጡት።

13. ከዚያም ሁለት የሐሰት ምስክሮች መጥተው ከፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ በሕዝቡም ፊት፣ “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል” ብለው መሰከሩበት። ስለዚህ ከከተማዪቱ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 21