ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 22:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ስለዚህ ዳዊት በእስራኤል የሚኖሩ መጻተኞች እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ከመካከላቸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ጥርብ ድንጋይ እንዲያዘጋጁ ጠራቢዎችን መደበ።

3. ለቅጥር በሮቹ ምስማርና ማጠፊያ የሚሆን ብዙ ብረትና ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስ አዘጋጀ።

4. እንዲሁም ሲዶናውያንና ጢሮሳውያን በብዛት አምጥተውለት ስለ ነበር፣ ስፍር ቍጥር የሌለው የዝግባ ዕንጨት አሰናዳ።

5. ዳዊትም፣ “ልጄ ሰሎሞን ወጣት ነው፤ ልምዱም የለውም፤ ለእግዚአብሔር የሚሠራው ቤተ መቅደስ ደግሞ እጅግ የሚያምር፣ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ ዝናው የተሰማና እጅግ የተዋበ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ሁሉንም እኔ አዘጋጃለሁ” አለ። እንዳለውም ዳዊት ከመሞቱ በፊት በብዛት አዘጋጀ።

6. ከዚያም ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሠራ አዘዘው።

7. ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፤ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ለመሥራት በልቤ አስብ ነበር፤

8. ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንዲህ የሚል ቃል መጣልኝ፤ “አንተ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ብዙ ጦርነትም አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም ያፈሰስህ ስለ ሆነ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራልኝም፤

9. ነገር ግን የሰላምና የዕረፍት ሰው የሆነ ልጅ ትወልዳለህ፤ በየአቅጣጫው ካሉ ጠላቶቹ ዐሳርፈዋለሁ፤ ስሙም ሰሎሞን ይባላል። በዘመኑም ለእስራኤል ሰላምንና ጸጥታን እሰጣለሁ።

10. ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ እርሱ ነው። እርሱ ልጅ ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ። ዙፋኑንም በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።

11. “አሁንም ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ እንድትፈጽመው በተናገረውም መሠረት፣ ተሳክቶልህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ያብቃህ።

12. በእስራኤል ላይ አለቃ ባደረገህ ጊዜ፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትፈጽም ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 22