ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 29:15-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው።

16. እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው።

17. አምላኬ ሆይ፤ ልብን እንደምትመረምርና ቅንነትን እንደምትወድ ዐውቃለሁ፤ እኔም ይህን ሁሉ የሰጠሁት በበጎ ፈቃድና በቀና መንፈስ ነው። አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በበጎ ፈቃዱ እንዴት እንደ ሰጠ አይቻለሁ።

18. የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ዐሳብ ለዘላለም በሕዝብህ ልብ ጠብቀው፤ ልባቸውንም ለአንተ ታማኝ አድርገው።

19. ትእዛዞችህን፣ ደንብህንና ሥርዐትህን እንዲጠብቅ፣ እኔ ባዘጋጀሁለት ነገሮች ታላቅ ሕንጻ ለመሥራት እንዲችል፣ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ፈቃደኝነት ስጠው።

20. ከዚያም ዳዊት ለመላው ጉባኤ፣ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱት” አላቸው። ስለዚህ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ወደሱ፤ በእግዚአብሔር በንጉሡም ፊት ተደፍተው ሰገዱ።

21. በማግስቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም አቀረቡ፤ ይህም አንድ ሺህ ወይፈን፣ አንድ ሺህ አውራ በግ፣ አንድ ሺህ የበግ ጠቦት ሲሆን፣ ከመጠጥ ቊርባኖቻቸውና ከሌሎች መሥዋዕቶች ጋር ስለ እስራኤል ሁሉ በብዛት አቀረቡ።

22. በዚያችም ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በታላቅ ደስታ በሉ፤ ጠጡም።ከዚያም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ዐወቁ፤ ገዥ እንዲሆንም በእግዚአብሔር ፊት ቀቡት፤ ሳዶቅንም ካህናቸው እንዲሆን ቀቡት።

23. ሰሎሞንም ነግሦ በአባቱ በዳዊት ምትክ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ተከናወነለት፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት።

24. የጦር አለቆቹና ኀያላኑ ሁሉ እንዲሁም የንጉሡ የዳዊት ወንዶች ልጆች በሙሉ ታማኝነታቸውን ለንጉሥ ሰሎሞን አረጋገጡለት።

25. እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ሁሉ እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከእርሱ በፊት ለነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ያላጐናጸፋቸውን ንጉሣዊ ክብር ሁሉ ሰጠው።

26. የእሴይ ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር።

27. እርሱም በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት፣ በአጠቃላይ አርባ ዓመት ነገሠ።

28. ብዙ ዘመን ባለጠግነትና ክብር ሳይጐድልበት ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ልጁ ሰሎሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

29. በንጉሥ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ድርጊት በባለ ራእዩ በሳሙኤል የታሪክ መጽሐፍ፣ በነቢዩ በናታን የታሪክ መጽሐፍ፣ በባለ ራእዩ በጋድ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።

30. የተጻፈውም በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ዝርዝር ጒዳዮችና በዙሪያው ከከበቡት፣ ከእስራኤልና ከሌሎች አገር መንግሥታት ታሪክ ጋር ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 29