ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 13:26-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. አቤሴሎምም፣ “እንግዲያውስ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ” አለው።ንጉሡም፣ “አብሮአችሁ የሚሄደው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

27. ነገር ግን አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ለመነው፣ አምኖንና ሌሎቹ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ሁሉ አብረውት እንዲሄዱ አደረገ።

28. አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፣ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ መንፈሱ መለወጡን ተጠባበቁ፤ ከዚያም እኔ አምኖንን፣ ‘ምቱት’ ስላችሁ ግደሉት፤ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ” ብሎ አዘዛቸው።

29. የአቤሴሎምም አገልጋዮች ጌታቸው ያዘዛቸውን በአምኖን ላይ ፈጸሙ። ከዚያም የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ።

30. እነርሱ በመንገድ ላይ ሳሉም፣ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው።

31. ንጉሡም ተነሥቶ ቆመ፤ ልብሱን ቀደደ፤ በመሬትም ላይ ተዘረረ፤ በአጠገቡ ቆመው የነበሩት አገልጋዮቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ።

32. የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “የንጉሡን ልጆች በሙሉ እንደ ፈጇቸው አድርጎ ጌታዬ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጊዜ አንሥቶ አቤሴሎም ቈርጦ የተነሣበት ጒዳይ ስለ ሆነ፣ የሞተው አምኖን ብቻ ነው።

33. እንግዲህ የሞተው አምኖን ብቻ ስለ ሆነ፣ ‘የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተገደሉ’ ተብሎ የተነገረውን ንጉሥ ጌታዬ ማመን የለበትም።”

34. አቤሴሎምም ፈጥኖ ሸሸ። ለዘብ ጥበቃ የቆመውም ሰው ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ከእርሱ በስተ ምዕራብ ካለው መንገድ ብዙ ሰዎች በተራራው ጥግ ቍልቍል ሲወርዱ አየ፤ ዘብ ጠባቂውም ሄዶ ለንጉሡ፣ “ከበስተ ሖሮናይም አቅጣጫ በኰረብታው ጥግ ላይ ሰዎች ቍልቍል ሲወርዱ አያለሁ” ብሎ ነገረው።

35. ኢዮናዳብም ዳዊትን፣ “እነሆ፣ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህም እንዳለው ሆኖአል” አለው።

36. ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የንጉሡ ልጆች ጮኸው እየተላቀሱ ገቡ፤ እንደዚሁም ንጉሡና አገልጋዮቹ ሁሉ እጅግ አለቀሱ።

37. አቤሴሎም ኰብልሎ የጌሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ፤ ነገር ግን ዳዊት ስለ ሞተው ልጁ ዘወትር ያለቅስ ነበር።

38. አቤሴሎም ሸሽቶ ወደ ጌሹር ከሄደ በኋላ፣ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 13