ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 15:13-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው።

14. ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው።

15. የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት።

16. ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ።

17. ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ።

18. ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ።

19. ንጉሡም ጌታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤

20. የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው።

21. ኢታይን ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል” ብሎ መለሰለት።

22. ዳዊትም ኢታይን፣ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይን ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ።

23. ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው ተጓዘ።

24. ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ አብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብብሔርን የኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ታቦት ዐሳረፉ፤ አብያታርም ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቆ እስኪወጣ ድረስ መሥዋዕት አቀረበ።

25. ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማዪቱ ይዘህ ተመለስ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን እንደ ገና ለማየት ያበቃኛል፤

26. ነገር ግን እርሱ፣ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፣ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ፤ እኔም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።”

27. እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? እንግዲህ አንተም ልጅህን አኪማአስን፣ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ።

28. እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቈያለሁ”

29. ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እዚያው ቈዩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 15