ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 19:22-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ዳዊትም፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ።

23. ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።

24. የሳኦል ልጅ ሜምፊቦስቴም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። ንጉሡ ከተሰደደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ ተገቢውን ጥንቃቄ አላደረገም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር።

25. እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

26. እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፣ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ ሲባ አታለለኝ።

27. በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የባሪያህን ስም አጥፍቶአል፤ መቼም ንጉሥ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንህ ደስ ያለህን ሁሉ አድርግ።

28. የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን ባሪያህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”

29. ንጉሡም፣ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ ዕርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው።

30. ሜምፊቦስቴም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 19