ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 19:26-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፣ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ ሲባ አታለለኝ።

27. በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የባሪያህን ስም አጥፍቶአል፤ መቼም ንጉሥ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንህ ደስ ያለህን ሁሉ አድርግ።

28. የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን ባሪያህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”

29. ንጉሡም፣ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ ዕርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው።

30. ሜምፊቦስቴም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።

31. እንዲሁም ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ዮርዳኖስን ተሻገረ።

32. በዚያን ጊዜ ቤርዜሊ በዕድሜ የገፋ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋ ስለ ነበረም ንጉሡ በመሃናይም ሳለ የሚመገበውን አምጥቶለት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 19