ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 21:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፣ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከ ወረደ ጊዜ ድረስ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤

11. የሳኦል ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፣

12. ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ወሰደ፤ የኢያቢስ ሰዎች፣ ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ ከገደሉ በኋላ እነርሱን ከሰቀሉት ከቤትሳን አደባባይ በድብቅ ወስደዋቸው ነበር።

13. ዳዊትም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አመጣ፤ እንዲሁም የእነዚያን የተገደሉትን ሰዎች ዐፅም ሰበሰቡ።

14. የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።

15. እንደ ገና በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተደረገ። ዳዊትም ከሰዎቹ ጋር ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወረደ፤ በዚያም ደከመው።

16. ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነ ይሽቢብኖብ የተባለ፣ የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል የሚመዝንና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ሰው ነበረ፤ እርሱም ዳዊትን ለመግደል አሰበ።

17. የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም ወግቶ ገደለው። ከዚያም የዳዊት ሰዎች፣ “የእስራኤል መብራት እንዳይጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት።

18. ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሌላ ጦርነት ተደረገ። በዚያን ጊዜም ኩሳታዊው ሴቦካይ፣ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነውን፣ ሳፍን ገደለው።

19. ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ሌላ ጦርነትም፣ የቤተ ልሔሙ የየዓሬዓርጊም ልጅ ኤልያናን፣ የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለው።

20. እንደ ገና ጌት ላይ በተደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች ባጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም ዘር ነበረ።

21. ይህም ሰው እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፣ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው።

22. እነዚህ አራቱ በጌት የራፋይም ዘሮች የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 21