ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 21:18-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሌላ ጦርነት ተደረገ። በዚያን ጊዜም ኩሳታዊው ሴቦካይ፣ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነውን፣ ሳፍን ገደለው።

19. ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ሌላ ጦርነትም፣ የቤተ ልሔሙ የየዓሬዓርጊም ልጅ ኤልያናን፣ የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለው።

20. እንደ ገና ጌት ላይ በተደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች ባጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም ዘር ነበረ።

21. ይህም ሰው እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፣ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው።

22. እነዚህ አራቱ በጌት የራፋይም ዘሮች የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 21