ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ።

2. እርሱና አብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በታቦቱ ላይ ባለው ኪሩቤል ላይ በተቀመጠው በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ወደ በአል ሄዱ።

3. የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፣ በኰረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአሚናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ሲሆኑ፣

4. የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፣ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር።

5. ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጽናጽልና በቃጭል ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር።

6. ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለ ተደናቀፉ፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእስራኤልን ታቦት ያዘ።

7. ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ።

8. የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛን ስለ ሰበረው፣ ዳዊት ተከፋ፤ አዘነም፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፔሬዝ ዖዛ ተብሎ ይጠራል።

9. ዳዊት በዚያን ቀን እግዚአብሔርን ስለ ፈራ “የእግዚአብሔር ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ።

10. ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት አብሮት እንዲሆን ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈለገም፤ በዚህ ፈንታ አቅጣጫ ለውጦ የጌት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው።

11. የእግዚአብሔርም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤተ ሰዉን ሁሉ ባረከ።

12. በዚህ ጊዜ፣ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የአቢዳራን ቤተ ሰውና ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር ባረከለት” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያው ወርዶ፣ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ አመጣው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 6