ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 8:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገሎች፣ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ሃያ ሺህ እግረኞች ማረከበት። ቊጥራቸው መቶ የሆነ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቈረጠ።

5. የደማስቆዎቹ ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለባቸው።

6. ከዚያም የደማስቆ ክፍል በሆነው የሶርያውያን ግዛት የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። ሶርያውያን ተገዙለት፤ ገበሩለትም። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው።

7. ዳዊት የአድርአዛር ሹማምንት ያነገቧቸውን የወርቅ ጋሻዎች ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው።

8. ንጉሡ ዳዊት ቤጣህና ቤሮታይ ከተባሉ ከአድርአዛር ከተሞችም እጅግ ብዙ ናስ አጋዘ።

9. የሐማት ንጉሥ ቶዑ ዳዊት መላውን የአድርአዛርን ሰራዊት ማሸነፉን በሰማ ጊዜ፣

10. ቶዑ ከአድርአዛር ጋር ሁል ጊዜ ይዋጋ ስለ ነበር፣ ሰላምታና በአድርአዛር ላይ ሰለተቀዳጀውም ድል የደስታ መግለጫ እንዲያቀርብለት፣ ልጁን ዮራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የብር፣ የወርቅና የናስ ዕቃ ይዞ መጣ።

11. ንጉሥ ዳዊትም፣ ቀድሞ ካስገበራቸው መንግሥታት ሁሉ በገባለት ብርና ወርቅ እንዳደረገው እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሳቸው።

12. የገበሩትም መንግሥታት ኤዶምና ሞዓብ፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያንና አማሌቃውያን ነበሩ። እንዲሁም ከሱባ ንጉሥ ከረአብ ልጅ ከአድርአዛር የወሰደውን ምርኮ ለእግዚአብሔር ቀደሰ።

13. ዳዊት የጨው ሸለቆ በተባለው ስፍራ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያንን ገድሎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ።

14. በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ኤዶማውያን ሁሉ ለዳዊት ተገዙ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን ሰጠው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 8