ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 4:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. አገልጋዩም አንሥቶ እናቱ ዘንድ አደረሰው፤ ልጁም እስከ እኩለ ቀን ድረስ በእናቱ ጭን ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ሞተ።

21. ወደ ላይ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው ዐልጋ ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታበት ወጣች።

22. ከዚያም ባሏን ጠርታ፣ “ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እንድመለስ አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ” አለችው።

23. ባሏም፣ “ዛሬ ወደ እርሱ መሄድ ለምን አስፈለገሽ? መባቻ ወይም ሰንበት አይደል” አላት።እርሷም፣ “ምንም አይደል፤ ልሂድ” አለችው።

24. ከዚያም አህያውን ጭና አገልጋይዋን፣ “ቶሎ ቶሎ ንዳ፤ እኔ ካልነገርኩህ በቀር ለእኔ ብለህ አታዝግም” አለችው።

25. ስለዚህ ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደች።የእግዚአብሔር ሰው በሩቁ ሲያያት አገልጋዩን ግያዝን እንዲህ አለው፤ “ሱነማዪቱን አየሃት፤ ያቻትና!

26. በል ሩጠህ ሂድና፣ ምነው ደኅና አይደለሽምን? ባልሽ ደኅና አይደለምን? ልጅሽስ ደህና አይደለምን? ብለህ ጠይቃት።”እርሷ፣ “ሁሉ ነገር ደህና ነው” አለች።

27. የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ተራራ ስትደርስም እግሩ ላይ ተጠመጠመች፤ ግያዝ ሊያስለቅቃት ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር ሰው ግን፣ “እጅግ አዝናለችና ተዋት! እግዚአብሔር ይህን ለምን ከእኔ እንደሰወረውና እንዳልነገረኝ አልገባኝም” አለ።

28. እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ለመሆኑ እኔ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‘አጒል ተስፋ እንዳትሰጠኝ’ አላልሁህምን?” አለችው።

29. ኤልሳዕም ግያዝን፣ “እንግዲህ ወገብህን ታጠቅ፤ በትሬን ያዝና ሩጥ፤ መንገድ ላይ ሰው ብታገኝ ሰላም አትበል፤ ማንም ሰው ሰላም ቢልህ መልስ አትስጥ፤ በትሬንም በልጁ ፊት ላይ አድርግ” አለው።

30. የልጁ እናት ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፣ ፈጽሞ ትቼህ አልሄድም” አለችው፤ ስለዚህ ተነሥቶ ተከተላት።

31. ግያዝም ቀድሞአቸው ሄዶ በትሩን በልጁ ፊት ላይ አደረገ፤ ነገር ግን ድምፅም፣ ምላሽም አልነበረም። ስለዚህ ግያዝ ወደ ኤልሳዕ ተመልሶ፣ “ልጁ አልነቃም” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 4