ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 9:30-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ከዚያም ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ኤልዛቤልም ይህን በሰማች ጊዜ ዐይኗን ተኳኵላ፣ ጠጒሯንም አሰማምራ በመስኮት ትመለከት ነበር።

31. ኢዩ የቅጥሩን በር አልፎ ሲገባ፣ “ጌታህን የገደልህ አንተ ዘምሪ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው።

32. ቀና ብሎ ወደ መስኮቱ ተመለከተና፣ “ማነህ አንተ? ማነው የሚተባበረኝ ሲል ጮኾ ተጣራ። ሁለት ሦስት ጃንደረቦችም ቊልቊል ወደ እርሱ ተመለከቱ፤

33. ኢዩም፣ “ወደ ታች ወርውሩአት!” አለ። እነርሱም ወረወሯት። ፈረሶቹ ሲረጋግጧትም ደሟ በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ።

34. ኢዩም ገብቶ በላ፤ ጠጣም። ከዚያም፣ “ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ናትና ይህችን የተረገመች ሴት በሚገባ ቅበሯት” አለ።

35. ሊቀብሯት ሲወጡ ግን ከራስ ቅሏ፣ ከእግሯና ከእጇ በቀር ሌላ ያገኙት አልነበረም።

36. ተመልሰውም ይህን ሲነግሩት፣ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ለባሪያው ለቴስቢያዊው ለኤልያስ፣ ‘በኢይዝራኤል ምድር ዕርሻ ውስጥ ውሾች የኤልዛቤልን ሥጋ ይበሉታል፤

37. ሥጋዋም በኢይዝራኤል ምድር ዕርሻ ውስጥ እንደ ፍግ ስለሚሆን፣ ማንም ሰው፣ ‘ይህች ኤልዛቤል ናት’ ሊል አይችልም ብሎ የተናገረው ቃል ይህ ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 9