ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 22:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዐረቦች ጋር ወደ ሰፈር የመጡት ወራሪዎች፣ ታላላቅ ወንድሞቹን ሁሉ ገድለዋቸው ስለ ነበር፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ የኢዮሆራምን የመጨረሻ ልጅ አካዝያስን በአባቱ ምትክ አነገሡት። ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ መግዛት ጀመረ።

2. አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የዘንበሪ የልጅ ልጅ ነበረች።

3. እናቱ ክፋትን እንዲያደርግ ትመክረው ስለ ነበር፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ።

4. ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለ መሩት፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

5. እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም የሶርያን ንጉሥ አዛሄል ለመውጋት ወደ ሬማት ገለዓድ በሄደ ጊዜ የእነዚህኑ ሰዎች ምክር ተከትሎ ከኢዮራም ጋር አብሮት ሄደ፣ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት።

6. ስለዚህ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር ባደረገው ጦርነት ሬማት ላይ ከደረሰበት ቍስል ለመዳን ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በመቍሰሉም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

7. አካዝያስ ኢዮራምን ለመጠየቅ መሄዱን፣ እግዚአብሔር ለአካዝያስ መውደቅ ምክንያት አደረገው፤ አካዝያስ እንደ ደረሰም የናሜሲን ልጅ ኢዩን ለመቀበል ከኢዮራም ጋር ወጣ፤ ኢዩም የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ እግዚአብሔር የቀባው ሰው ነበር።

8. ኢዩ በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድ በሚፈጽምበት ጊዜ፣ አካዝያስን ያጅቡ የነበሩትን የይሁዳን መሳፍንትና የዘመዶቹን ወንዶች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 22