ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 26:2-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አሜስያስ እንደ አባቶቹ ሁሉ ካንቀላፋ በኋላ፣ ኤላትን እንደ ገና የሠራት፣ ወደ ይሁዳም የመለሳት ዖዝያን ነበር።

3. ዖዝያን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

4. እርሱም አባቱ አሜስያስ እንደ አደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።

5. እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።

6. በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጌትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ።

7. እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን፣ በጉርበኣል በሚኖሩ ዐረቦችና በምዑናውያን ላይ ድልን አቀዳጀው።

8. አሞናውያን ለዖዝያን ግብር ገበሩለት፤ ኀይሉ ስለ ገነነም ዝናው እስከ ግብፅ ዳርቻ ወጣ።

9. ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በር፣ በሸለቆው በርና በቅጥሩ ማዕዘን ማማዎች ሠርቶ መሸጋቸው።

10. እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጒድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሰራተኞች ነበሩት።

11. ዖዝያን ከንጉሡ ሹማምት አንዱ በሆነው በሐናንያ መሪነት፣ በጸሓፊው በይዒኤልና በአለቃው በመዕሤያ አማካይነት ተሰብስቦ በተቈጠረው መሠረት በየምድቡ ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ የሚወጣ፣ በሚገባ የሠለጠነ ሰራዊት ነበረው።

12. በተዋጊዎቹ ላይ የተሾሙት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ጠቅላላ ቊጥር ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር።

13. በእነዚህም የሚመራ ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሰው ያለው ሰራዊት አለ፤ ይህም ንጉሡ በጠላቶቹ ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ለመሰለፍ የሚበቃ ጠንካራ ኃይል ነበር።

14. ዖዝያን ለሰራዊቱ ሁሉ ጋሻ፣ ጦር፣ የራስ ቁር፣ ጥሩር፣ የቀስት ማስፈንጠሪያ ደጋንና የሚወነጨፍ ድንጋይ አደለ።

15. በኢየሩሳሌምም፣ ንድፎቻቸው በባለ ሙያዎች የተዘጋጁ፣ በመጠበቂያ የግንብ ማማዎችና በየማዕዘኑ መከላከያዎች ላይ ፍላጻ የሚስፈነጠርባቸውንና ትልልቅ ድንጋዮች የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አሠራ። እስኪበረታም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለታገዘ፣ ዝናው በርቀትና በስፋት ተሰማ።

16. ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ እግዚአብሔርን በደለ፤

17. ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋር ተከትሎት ገባ።

18. እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 26