ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 29:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. አባቶቻችን ታማኞች አልነበሩም፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ተውትም። ከእግዚአብሔር ማደሪያ ፊታቸውን መለሱ፤ ጀርባቸውንም አዞሩበት።

7. የሰበሰቡንም በሮች ዘጉ፤ መብራቶቹንም አጠፉ። ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ዕጣን አላጠኑም፤ በመቅደሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አላቀረቡም።

8. ስለዚህ የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወርዶአል፤ እናንተ በገዛ ዓይናችሁ እንደምታዩት ለድንጋጤ፣ ለመደነቂያና ለመዘበቻ አሳልፎ ሰጣቸው።

9. በዚህ ምክንያት አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፣ ሚስቶቻችንም ተማረኩ።

10. አሁንም አስፈሪ ቊጣው ከእኛ እንዲመለስ፣ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት አስቤአለሁ።

11. ልጆቼ ሆይ፤ እንግዲህ ቸል አትበሉ፤ በፊቱ እንድትቆሙና እንድታገለግሉት፣ በፊቱም አገልጋዮቹ እንድትሆኑና ዕጣን እንድ ታጥኑለት እግዚአብሔር መርጦአችኋልና።”

12. ከዚያም እነዚሁ ሌዋውያን በሥራው ላይ ተሰማሩ፤ ከቀዓት ዘሮች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፤ከሜራሪ ዘሮች፣የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፤ከጌድሶን ዘሮች፣የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፤

13. ከኤሊጻፋን ዘሮች፣ሺምሪና ይዒኤል፤ከአሳፍ ዘሮች፣ዘካርያስና መታንያ፤

14. ከኤማን ዘሮች፣ይሒኤልና ሰሜኢ፣ከኤዶታም ዘሮች፣ሸማያና ዑዝኤል።

15. ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ፣ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ቃል ተከትሎ ባዘዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማንጻት ገቡ።

16. ካህናቱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትንም ማናቸውንም የረከሰ ነገር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ አወጡት። ሌዋውያኑም ተሸክመው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 29