ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 13:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት በሚናገሩት በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ከገዛ ራሳቸው ትንቢት የሚናገሩትን እንዲህ በላቸው፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

3. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አንዳች ነገር ሳያዩ የራሳቸውን መንፈስ ለሚከተሉ ሞኞች ነቢያት ወዮላቸው!

4. እስራኤል ሆይ፤ ነቢያትሽ በፍርስራሽ መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው።

5. በእግዚአብሔር ቀን በሚሆነው ጦርነት ጸንቶ መቆም እንዲችል፣ የተሰነጠቀውን ቅጥር ለእስራኤል ቤት ለመጠገን ወደዚያ አልወጣችሁም።

6. ራእያቸው ሐሰት፣ ትንቢታቸው ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ፤ ይህም ሆኖ የተናገሩት ይፈጸማል ብለው ይጠብቃሉ።

7. እኔ ሳልናገር፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ስትሉ ሐሰተኛ ራእይ ማየታችሁ፣ ውሸተኛስ ትንቢት መናገራችሁ አይደለምን?”

8. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃላችሁ ሐሰት፣ ራእያችሁም ውሸት ስለ ሆነ እኔ በእናንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

9. እጄ የሐሰት ራእይ በሚያዩና በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ ተነሥቶአል። የሕዝቤ ጉባኤ ተካፋይ አይሆኑም፤ በእስራኤል ቤት መዝገብ አይጻፉም፤ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም። በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

10. “ሰላም ሳይኖር፣ ‘ሰላም አለ’ እያሉ ሕዝቤን ያስታሉ፤ ሕዝቡ ካብ ሲሠራ እነርሱ በኖራ ይለስናሉ፤

11. ስለዚህ በኖራ ለሚለስኑት ካቡ እንደሚወድቅ ንገራቸው። ዶፍ ይወርዳል፤ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ እሰዳለሁ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል።

12. እነሆ ካቡ ሲፈርስ ሕዝቡ ‘የለሰናችሁበት ኖራው ወዴት ሄደ?’ ብለው አይጠይቋችሁምን?”

13. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመዓቴ ዐውሎ ነፋስ እሰዳለሁ፣ በቍጣዬ የበረዶ ድንጋይ እልካለሁ፤ ዶፍም ከታላቅ ጥፋት ጋር ይወርዳል።

14. በኖራ የለሰናችሁትን ካብ አፈርሳለሁ፤ መሠረቱም ተገልጦ እስኪታይ ድረስ ከምድር ጋር አደባልቀዋለሁ። ቅጥሩ በሚወድቅበት ጊዜ፣ እናንተም በውስጡ ታልቃላችሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 13