ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 30:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. በግብፅ ላይ እሳት አነዳለሁ፤ሲን በጭንቅ ትናጣለች፤ቴብስ በማዕበል ትወሰዳለች፤ሜምፊስ በማያቋርጥ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች።

17. የሄልዮቱና የቡባስቱ ጐልማሶች፣በሰይፍ ይወድቃሉ፤ከተሞቹ ራሳቸውም ይማረካሉ።

18. የግብፅን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፣በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል፤ከዚያም የተኵራራችበት ብርታት ይንኰታኰታል።በደመና ትሸፈናለች፤መንደሮቿም ይማረካሉ።

19. ስለዚህ በግብፅ ላይ ቅጣቴን አመጣለሁ፤እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

20. በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21. “የሰው ልጅ ሆይ፤ የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ ይፈወስ ዘንድ ክንዱ አልተጠገነም፤ ወይም ሰይፍ መያዝ ይችል ዘንድ እጁ በመቃ አልታሰረም።

22. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ተነሥቻለሁ፤ ደኅናውንና የተሰበረውን፣ ሁለቱንም ክንዶቹን እሰብራለሁ፤ ሰይፉም ከእጁ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።

23. ግብፃውያንን በሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።

24. የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ ሰይፌንም አስይዘዋለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፤ እርሱም በፊቱ ክፉኛ እንደ ቈሰለ ሰው ያቃስታል።

25. የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ የፈርዖን ክንድ ግን ይዝላል፤ ሰይፌን በባቢሎን ንጉሥ እጅ ሳስይዝ፣ እርሱም ሲነቀንቀው፣ ያኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 30