ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 43:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በር አመጣኝ፤

2. እኔም የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ ድምፁ እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ነበር፤ ምድሪቱም ከክብሩ የተነሣ ታበራ ነበር።

3. ያየሁትም ራእይ ከተማዪቱን ለማጥፋት በመጣ ጊዜ ያየሁትን ራእይ የሚመስልና እንዲሁም በኮቦር ወንዝ ካየሁት ራእይ ጋር የሚመሳሰል ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ።

4. የእግዚአብሔር ክብር ለምሥራቅ ትይዩ በሆነው በር ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ።

5. ከዚያም መንፈስ አነሣኝ፤ ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው።

6. ያ ሰው በአጠገቤ ቆሞ ሳለ፣ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲናገረኝ ሰማሁ፤

7. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ የእግሬም ጫማ ማሳረፊያ ነው፤ በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም የምኖርበትም ስፍራ ነው። የእስራኤል ቤትም ሆኑ ነገሥታታቸው በአመንዝራነታቸውና በማምለኪያ ኰረብታቸው ላይ በሚያመልኳቸው፣ ሕይወት በሌላቸው በነገሥታታቸው ጣዖታት ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።

8. በእኔና በጣዖታቱ መካከል ግንብ ብቻ ሲቀር፣ መድረኮቻቸውን ከመድረኬ አጠገብ፣ መቃኖቻቸውን ከመቃኖቼ አጠገብ በማድረግ፣ በአስጸያፊ ድርጊታቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው።

9. ከእንግዲህ አመንዝራነታቸውንና ሕይወት የሌላቸውን የንጉሦቻቸውን ጣዖታት ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።

10. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ኀጢአታቸው ያፍሩ ዘንድ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ቤተ መቅደሱን አሳያቸው፤ ንድፉንም ያስተውሉ፤

11. ስላደረጉት ነገር ሁሉ ኀፍረት የሚሰማቸው ከሆነ፣ የቤተ መቅደሱን ንድፍ እንዲያውቁት አድርግ፤ ይኸውም አሠራሩን፣ መውጫና መግቢያውን፣ አጠቃላይ ንድፉን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ነው። ንድፉንና ሥርዐቱን እንዲጠብቁና እንዲከተሉ እነዚህን ሁሉ እነርሱ ባሉበት ጻፋቸው።

12. “የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ አካባቢ ያለው ስፍራ ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። የቤተ መቅደሱም ሕግ ይኸው ነው።

13. “የመሠዊያው ልክ በረጅም ክንድ ይህ ነው፤ ይኸውም ክንድ ከስንዝር ማለት ነው፤ ቦዩ አንድ ክንድ ጥልቀት፣ አንድ ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ዙሪያው አንድ ስንዝር ጠርዝ አለው፤ የመሠዊያውም ከፍታ ይህ ነው፤

14. ከቦዩ መሠረት አንሥቶ እስከታችኛው ዕርከን ድረስ ሁለት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ከትንሹ ዕርከን አንሥቶ እስከ ትልቁ ዕርከን ድረስ ደግሞ አራት ክንድ ቁመት፣ አንድ ክንድ ወርድ አለው።

15. የመሠዊያው ምድጃ ከፍታው አራት ክንድ ሲሆን፣ ከምድጃው ወጣ ወጣ ያሉ አራት ቀንዶች አሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 43