ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 44:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. በራሳቸው ላይ ከበፍታ ፈትል የተሠራ ጥምጥም ያድርጉ፤ እንዲሁም ከበፍታ ፈትል የተሠራ ሱሪ በወገባቸው ላይ ይታጠቁ፤ እንዲያልባቸው የሚያደርግ ማንኛውንም ልብስ አይልበሱ።

19. ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ውጩ አደባባይ ሲወጡ፣ ሲያገለግሉበት የነበረውን ልብስ አውልቀው በተቀደሱት ክፍሎች በመተው ሌሎች ልብሶችን ይልበሱ፤ ይኸውም ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ነው።

20. ‘ “የራሳቸውን ጠጒር አይላጩት፤ ወይም አያርዝሙት፤ ነገር ግን ይከርክሙት።

21. ማንኛውም ካህን ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጣ።

22. መበለቶችን ወይም ፈት ሴቶችን አያግቡ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ዘር የሆኑ ድንግሎችን ወይም የካህናት ሚስቶች የነበሩትን መበለቶች ማግባት ይችላሉ።

23. በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ያለውን ልዩነት ለሕዝቤ ያስተምሩ፤ የረከሰውንና ያልረከሰውን እንዴት እንደሚለዩም ያሳዩአቸው።

24. ‘ “በማንኛውም ክርክር ካህናት ዳኞች ሆነው ያገልግሉ፤ በሥርዐቴም መሠረት ይወስኑ። የተለዩ በዓላቴን የሚመለከቱ ሕጎቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ ይጠብቁ፤ ሰንበታቴንም ቅዱስ አድርገው ይጠብቁ።

25. ‘ “ካህን ወደ ሞተ ሰው ሬሳ በመጠጋት ራሱን አያርክስ፤ ይሁን እንጂ ሟች አባቱ ወይም እናቱ፣ ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ፣ ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ብትሆን፣ ራሱን ማርከስ ይችላል።

26. ከነጻም በኋላ፣ ሰባት ቀን መቈየት አለበት።

27. በመቅደሱ ለማገልገል፣ ወደ መቅደሱ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ቀን፣ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

28. ‘ “ለካህናቱ ርስታቸው እኔ ብቻ ነኝ፤ በእስራኤል ምንም ዐይነት ርስት አትስጧቸው፤ እኔ ርስታቸው እሆናለሁ።

29. የእህሉን ቍርባን፣ የኀጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕትይበላሉ፤ በእስራኤል ለእግዚአብሔር የተሰጠው ሁሉ የእነርሱ ይሆናል።

30. ከፍሬ በኵራት ምርጥ የሆነው ሁሉ እንዲሁም ከልዩ ስጦታዎቻችሁ የመጀመሪያው ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ ለቤተ ሰዎቻችሁ ሁሉ በረከት እንዲሆን ከምድር የምታገኙትን መብል በኵራት ለእነርሱ ስጧቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 44