ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 107:26-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ወደ ሰማይ ወጡ፤ ወደ ጥልቅም ወረዱ፤ከመከራቸውም የተነሣ ሐሞታቸው ፈሰሰ።

27. እንደ ሰከረ ሰው ዞሮባቸው ወዲያ ወዲህ ተንገዳገዱ፤መላው ጠፍቶባቸው የሚያደርጉትን አጡ።

28. በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።

29. ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ አደረገ፤የባሕሩም ሞገድ ረጭ አለ።

30. ጸጥ በማለቱም ደስ አላቸው፤ወዳሰቡትም ወደብ አደረሳቸው።

31. እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤

32. በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፤በሽማግሌዎችም ሸንጎ ይወድሱት።

33. ወንዞችን ወደ ምድረ በዳ፣የውሃ ምንጮችንም ወደ ደረቅ ምድር ለወጠ።

34. ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ፣ፍሬያማዋን ምድር በጨው የተበከለች አደረጋት።

35. ምድረ በዳውን ወደ ውሃ መከማቻ፣ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ።

36. የተራቡትን በዚያ አስቀመጠ፤የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ።

37. በዕርሻውም ዘሩበት፤ ወይንም ተከሉ፤ብዙ ፍሬም አመረቱ።

38. ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም።

39. በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣ቍጥራቸው አንሶ፣ ተዋርደው ነበር፤

40. በመኳንንቱም ላይ መናቅን አዘነበባቸው፤መውጫ መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥም አንከራተታቸው።

41. ችግረኞችን ግን ከጭንቀታቸው መዝዞ አወጣቸው፤ቤተ ሰባቸውንም እንደ በግ መንጋ አበዛ።

42. ልበ ቅኖች ይህን አይተው ሐሤት ያደርጋሉ፤ጥመትም ሁሉ አፏን ትዘጋለች።

43. እንግዲህ ማንም ብልህ ቢሆን፣ ይህን ነገር ልብ ይበል፤እርሱም የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 107