ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 107:6-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።

7. ወደሚኖሩባትም ከተማ፣በቀና መንገድ መራቸው።

8. እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤

9. እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቶአልና፤የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቦአል።

10. አንዳንዶቹ በብረት ሰንሰለት ታስረው የተጨነቁ፣በጨለማ፣ በጥልማሞት ውስጥ የተቀመጡ ነበሩ፤

11. በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማመፅ፣የልዑልን ምክር አቃለዋልና።

12. ስለዚህ በጒልበት ሥራ ልባቸውን አዛለ፤ተዝለፈለፉ፤ የሚደግፋቸውም አልነበረም።

13. በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።

14. ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤እስራታቸውንም በጠሰላቸው።

15. እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤

16. እርሱ የናሱን በሮች ሰብሮአልና፤የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአል።

17. አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ።

18. ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።

19. በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።

20. ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው።

21. እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ፣ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤

22. የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ።

23. አንዳንዶቹ በመርከብ ወደ ባሕር ወረዱ፤በታላቅም ውሃ ላይ ሥራቸውን አከናወኑ፤

24. የእግዚአብሔርን ሥራ በዚያ አዩ፤ድንቅ አድራጎቱንም በጥልቁ ውስጥ ተመለከቱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 107