ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 118:17-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤ የእግዚአብሔርንም ሥራ ገና እናገራለሁ።

18. መገሠጹን እግዚአብሔር እጅግ ገሥጾኛል፤ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም።

19. የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።

20. ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ጻድቃን በእርሷ በኩል ይገባሉ።

21. ሰምተህ መልሰህልኛልና፣አዳኝም ሆነህልኛልና አመሰግንሃለሁ።

22. ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።

23. እግዚአብሔር ይህን አደረገ፤ለዐይናችንም ድንቅ ናት።

24. እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤በእርሷ ሐሤት እናድርግ፤ ደስም ይበለን።

25. እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አድነን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አሳካልን።

26. በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው። ከእግዚአብሔር ቤት ባረክናችሁ።

27. እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ብርሃኑንም በላያችን አበራ፤እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ በመውጣት፣ዝንጣፊ ይዛችሁ በዓሉን ከሚያከብሩት ጋር ተቀላቀሉ።

28. አንተ አምላኬ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ፤አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።

29. ቸር ነውና፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 118