ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48
  49. 49
  50. 50
  51. 51
  52. 52
  53. 53
  54. 54
  55. 55
  56. 56
  57. 57
  58. 58
  59. 59
  60. 60
  61. 61
  62. 62
  63. 63
  64. 64
  65. 65
  66. 66
  67. 67
  68. 68
  69. 69
  70. 70
  71. 71
  72. 72
  73. 73
  74. 74
  75. 75
  76. 76
  77. 77
  78. 78
  79. 79
  80. 80
  81. 81
  82. 82
  83. 83
  84. 84
  85. 85
  86. 86
  87. 87
  88. 88
  89. 89
  90. 90
  91. 91
  92. 92
  93. 93
  94. 94
  95. 95
  96. 96
  97. 97
  98. 98
  99. 99
  100. 100
  101. 101
  102. 102
  103. 103
  104. 104
  105. 105
  106. 106
  107. 107
  108. 108
  109. 109
  110. 110
  111. 111
  112. 112
  113. 113
  114. 114
  115. 115
  116. 116
  117. 117
  118. 118
  119. 119
  120. 120
  121. 121
  122. 122
  123. 123
  124. 124
  125. 125
  126. 126
  127. 127
  128. 128
  129. 129
  130. 130
  131. 131
  132. 132
  133. 133
  134. 134
  135. 135
  136. 136
  137. 137
  138. 138
  139. 139
  140. 140
  141. 141
  142. 142
  143. 143
  144. 144
  145. 145
  146. 146
  147. 147
  148. 148
  149. 149
  150. 150

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 119 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ውዳሴ ለሕገ እግዚአብሔር

1. መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።

2. ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው፤

3. ዐመፅን አያደርጉም፤ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ።

4. ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣አንተ ሥርዐትን አዘሃል።

5. ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ!

6. ወደ ትእዛዛትህ ስመለከት፣በዚያን ጊዜ አላፍርም።

7. የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።

8. ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ፈጽመህ አትተወኝ።

9. ጒልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል?በቃልህ መሠረት በመኖር ነው።

10. በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ከትእዛዛትህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ።

11. አንተን እንዳልበድል፣ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።

12. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።

13. ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣በከንፈሬ እናገራለሁ።

14. ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል።

15. ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ።

16. በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ቃልህንም አልዘነጋም።

17. ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ለአገልጋይህ መልካም አድርግ።

18. ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ዐይኖቼን ክፈት።

19. እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር።

20. ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ነፍሴ እጅግ ዛለች።

21. ከትእዛዛትህ የሳቱትን፣እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ።

22. ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ።

23. ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል።

24. ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤መካሪዬም ነው።

25. ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

26. ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።

27. የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።

28. ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤እንደ ቃልህ አበርታኝ።

29. የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ።

30. የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ።

31. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋር ተጣብቄአለሁ፤አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ።

32. ልቤን አስፍተህልኛልና፣በትእዛዛትህ መንገድ እሮጣለሁ።

33. እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ።

34. ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ።

35. በእርሷ ደስ ይለኛልና፣በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ።

36. ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል።

37. ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ።

38. ትፈራ ዘንድ፣ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም።

39. የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤ደንብህ መልካም ነውና።

40. እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ።

41. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ።

42. በቃልህ ታምኛለሁና፣ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ።

43. ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።

44. ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ።

45. ሥርዐትህን እሻለሁና፣እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ።

46. ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም።

47. እኔ እወደዋለሁና፣በትእዛዝህ ደስ ይለኛል።

48. እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ።

49. ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና።

50. ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።

51. እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም።

52. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን ዐሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ።

53. ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ቍጣ ወረረኝ።

54. በእንግድነቴ አገር፣ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት።

55. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ሕግህንም እጠብቃለሁ።

56. ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ይህችም ተግባሬ ሆነች።

57. እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ።

58. በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ።

59. መንገዴን ቃኘሁ፤አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።

60. ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም።

61. የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም።

62. ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ።

63. እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።

64. እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።

65. እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል።

66. በትእዛዛትህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትንአስተምረኝ።

67. እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ።

68. አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ።

69. እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ።

70. ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።

71. ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ።

72. ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።

73. እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ትእዛዛትህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።

74. ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው።

75. እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደሆነ ዐወቅሁ።

76. ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ።

77. ሕግህ ደስታዬ ነውና፣በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ።

78. እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አሰላስላለሁ።

79. አንተን የሚፈሩህ፣ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።

80. እኔ እንዳላፍር፤ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።

81. ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

82. “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።

83. ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ሥርዐትህን አልረሳሁም።

84. የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው?ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን?

85. በሕግህ መሠረት የማይሄዱ፣እብሪተኞች ማጥመጃ ጒድጓድ ቈፈሩልኝ።

86. ትእዛዛትህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ሰዎች ያለ ምክንያት አሳደውኛልና ርዳኝ።

87. ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።

88. እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ።

89. እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

90. ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።

91. ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ።

92. ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር።

93. በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም።

94. እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ሕግህንም ፈልጌአለሁና።

95. ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ።

96. ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።

97. አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።

98. ትእዛዛትህ ምንጊዜም ስለማይለዩኝ፣ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ።

99. ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ።

100. መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ።

101. ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።

102. አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም።

103. ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው!ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው።

104. ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

105. ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ለመንገዴም ብርሃን ነው።

106. የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ።

107. እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

108. እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፤ሕግህንም አስተምረኝ።

109. ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ሕግህን ግን አልረሳሁም።

110. ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም።

111. ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና።

112. ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ።

113. መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ሕግህን ግን ወደድሁ።

114. አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ።

115. የአምላኬን ትእዛዛት እጠብቅ ዘንድ፣እናንት ክፉ አድራጊዎች፣ ከእኔ ራቁ።

116. እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር።

117. ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ።

118. መሰሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው።

119. የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።

120. ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ፍርድህንም እፈራለሁ።

121. ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።

122. ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤እብሪተኛ እንዲጨቍነኝ አትፍቀድላቸው።

123. ዐይኖቼ ማዳንህን፣የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።

124. ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ሥርዐትህንም አስተምረኝ።

125. እኔ ባሪያህ ነኝ፤ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።

126. እግዚአብሔር ሆይ፤ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው።

127. ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ትእዛዛትህን ወደድሁ።

128. መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

129. ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች።

130. የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል።

131. ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም።

132. ስምህን ለሚወዱ ማድረግ ልማድህ እንደሆነ ሁሉ፣ወደ እኔ ተመልሰህ፣ ምሕረት አድርግልኝ።

133. አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ።

134. ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ።

135. በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ሥርዐትህንም አስተምረኝ።

136. ሕግህ ባለመከበሩ፤እንባዬ እንደ ውሃ ይፈሳል።

137. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ፍርድህም ትክክል ነው።

138. ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤እጅግ አስተማማኝም ነው።

139. ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ቅናት አሳረረኝ።

140. ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ባሪያህም ወደደው።

141. እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም።

142. ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ሕግህም እውነት ነው።

143. መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው።

144. ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።

145. እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ።

146. ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ።

147. ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

148. ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል።

149. እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

150. ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው።

151. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ትእዛዛትህም ሁሉ እውነት ናቸው።

152. ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ።

153. ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም።

154. ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ።

155. ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው።

156. እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ።

157. የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም።

158. ቃልህን አይጠብቁምና፣ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ።

159. መመሪያህን እንዴት እንደምወድ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ።

160. ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው።

161. ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ።

162. ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፤በቃልህ ደስ አለኝ።

163. ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ሕግህን ግን ወደድሁ።

164. ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፤በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ።

165. ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ዕንቅፋትም የለባቸውም።

166. እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ።

167. ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤እጅግ እወደዋለሁና።

168. መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ።

169. እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ።

170. ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤እንደ ቃልህም ታደገኝ።

171. ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ።

172. ትእዛዛትህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዛት ናቸውና፣አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር።

173. ትእዛዝህን መርጫለሁና፣እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን።

174. እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ሕግህም ደስታዬ ነው።

175. አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ሕግህም ይርዳኝ።

176. እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ትእዛዛትህን አልረሳሁምና፣ባሪያህን ፈልገው።