ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 34:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።

5. ወደ እርሱ የሚመለከቱ ያበራሉ፤ፊታቸውም ከቶ አያፍርም።

6. ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ከመከራውም ሁሉ አዳነው።

7. እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ያድናቸዋልም።

8. እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!

9. እናንተ ቅዱሳኑ፤ እግዚአብሔርን ፍሩት፤እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።

10. አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም።

11. ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።

12. ሕይወትን የሚወድ፣በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው?

13. አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ።

14. ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም።

15. የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።

16. መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት፣ የእግዚአብሔር ፊት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።

17. ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል።

18. እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።

19. የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 34