ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 64:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት።

2. ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤ከዐመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ።

3. እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ።

4. አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል፤ድንገት ይነድፉታል፤ አይፈሩምም።

5. ክፉ ተግባር ለማከናወን እርስ በርስ ይመካከራሉ፤በስውር ወጥመድ ለመዘርጋት ይነጋገራሉ፤“ማንስ ሊያየን ይችላል?” ይባባላሉ።

6. ግፍን ያውጠነጥናሉ፤ደግሞም፣ “የረቀቀች ሤራ አዘጋጅተናል” ይላሉ፤አቤት! ልቡ፣ አእምሮውም እንዴት ጥልቅ ነው!

7. እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ።

8. በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤ጥፋትንም ያመጣባቸዋል፤የሚያዩአቸውም ሁሉ በትዝብት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።

9. የሰው ልጆች ሁሉ ይፈራሉ፤የእግዚአብሔርን ሥራ በይፋ ያወራሉ፤ያደረገውንም በጥሞና ያሰላስላሉ።

10. ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይበለው፤እርሱንም መጠጊያ ያድርገው፤ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 64