ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 69:17-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ፊትህን ከባሪያህ አትሰውር፤ጭንቅ ውስጥ ነኝና ፈጥነህ መልስልኝ።

18. ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ።

19. የደረሰብኝን ስድብ፣ ዕፍረትና ውርደት ታውቃለህ፤ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ።

20. ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ተስፋዬም ተሟጦአል፤አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም።

21. ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ።

22. የቀረበላቸው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው፤ለማኅበራቸውም አሽክላ ይሁን።

23. ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ጀርባቸውም ዘወትር ይጒበጥ።

24. መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤የቍጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው።

25. ሰፈራቸው ባድማ ይሁን፤በድንኳኖቻቸው የሚኖር አይገኝ፤

26. አንተ የመታኻቸውን አሳደዋልና፤ያቈሰልኻቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል።

27. በበደላቸው በደል ጨምርባቸው፤ወደ ጽድቅህም አይግቡ።

28. ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰሱ፤ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።

29. ነገር ግን እኔ በሥቃይና በጭንቅ ላይ እገኛለሁ፤አምላክ ሆይ፤ ማዳንህ ደግፎ ይያዘኝ።

30. የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አወድሳለሁ፤በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።

31. ከበሬ ይልቅ፣ቀንድና ጥፍር ካበቀለ እምቦሳም ይልቅ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።

32. ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ ልባችሁ ይለምልም!

33. እግዚአብሔር ችግረኞችን ይሰማልና፤በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 69