ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 73:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “ለመሆኑ እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል?በልዑልስ ዘንድ ዕውቀት አለ?” ይላሉ።

12. እንግዲህ፣ ክፉዎች ይህን ይመስላሉ፤ሁል ጊዜ ግድ የለሽና ሀብት በሀብት ናቸው።

13. ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል!

14. ቀኑን ሙሉ ተቀሠፍሁ፤ጠዋት ጠዋትም ተቀጣሁ።

15. “እኔ እንደዚህ እናገራለሁ” ብልማ ኖሮ፣የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር።

16. ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ።

17. ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር።

18. በእርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፤ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው።

19. እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ!በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ።

20. ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ።

21. ነፍሴ በተማረረች ጊዜ፣ልቤም በተቀሠፈ ጊዜ፣

22. ስሜት የሌለውና አላዋቂ ሆንሁ፤በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ።

23. ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፤አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል።

24. በምክርህ መራኸኝ፤ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 73