ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 89:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እግዚአብሔር በቅዱሳን ጉባኤ መካከል በጣም የሚፈራ፣በዙሪያውም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የሚከበር ነው።

8. የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ታማኝነትህም ከብቦሃል።

9. የባሕርን ቍጣ ትቈጣጠራለህ፤ሞገዱም ሲነሣ ጸጥ ታደርገዋለህ።

10. አንተ ረዓብን የተሰየፈ ያህል አደቀቅኸው፤በብርቱ ክንድህም ጠላቶችህን በተንሃቸው።

11. ሰማያት የአንተ ናቸው፤ ምድርም የአንተ ናት፤ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አንተ መሠረትህ።

12. ሰሜንንና ደቡብን የፈጠርህ አንተ ነህ፤ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ሐሤት ያደርጋሉ።

13. አንተ ክንደ ብርቱ ነህ፤እጅህ ኀያል ናት፤ ቀኝ እጅህም ከፍ ከፍ ያለች ናት።

14. ጽድቅና ፍትሕ የዙፋንህ መሠረቶች ናቸው፤ምሕረትና ታማኝነት በፊትህ ይሄዳሉ።

15. እግዚአብሔር ሆይ፤ እልልታን የሚያውቅ፣በፊትህም ብርሃን የሚሄድ ሕዝብ ምስጉን ነው።

16. ቀኑን ሙሉ በስምህ ደስ ይላቸዋል፤በጽድቅህም ሐሤት ያደርጋሉ፤

17. አንተ የብርታታቸው ክብር ነህና፤በሞገስህም ቀንዳችንን ከፍ ከፍ አደረግህ።

18. ጋሻችን የእግዚአብሔር ነውና፤ንጉሣችንም የራሱ የእስራኤል ቅዱስ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 89