ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መዝሙር 94:3-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ክፉዎች እስከ መቼ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ?

4. የእብሪት ቃላት ያዥጐደጒዳሉ፤ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጒራ ይነዛሉ።

5. እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤ርስትህንም አስጨነቁ።

6. መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ።

7. እነርሱም “እግዚአብሔር አያይም፤የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ።

8. እናንት በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤እናንት ቂሎች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?

9. ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?

10. ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?

11. እግዚአብሔር የሰው ሐሳብ መና፣ከንቱም እንደሆነ ያውቃል።

12. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣ከሕግህም የምታስተምረው ሰው ምስጉን ነው።

13. ለኀጢአተኞች ጒድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ።

14. እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤ርስቱንም አይተውም።

15. ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል።

16. ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው?ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር የሚሟገትልኝ ማን ነው?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መዝሙር 94