ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 5:11-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እናንተ ድኻውን ትረግጣላችሁ፤እህል እንዲሰጣችሁም ታስገድዱታላችሁ፤ስለዚህ በተጠረበ ድንጋይ ቤት ብትሠሩም፣በውስጡ ግን አትኖሩም፤ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች ወይን ብትተክሉም፣የወይን ጠጁን ግን አትጠጡም፤

12. ኀጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደሆነ፣በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና።ጻድቁን ትጨቊናላችሁ፤ጒቦም ትቀበላላችሁ፤በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።

13. ስለዚህ አስተዋይ ሰው በእንዲህ ያለ ጊዜ ዝም ይላል፤ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና።

14. በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፣መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ከዚያ በኋላ እንደ ተናገራችሁት፣የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።

15. ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር፣ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።

16. ስለዚህ ጌታ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በየመንገዱ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤በአደባባዩም የሥቃይ ጩኸት ይሆናል፤ ገበሬዎች ለልቅሶ፣አልቃሾችም ለዋይታ ይጠራሉ።

17. በየወይኑ ዕርሻ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤እኔ በመካከላችሁ አልፋለሁና፤”ይላል እግዚአብሔር።

18. የእግዚአብሔርን ቀን ለምትሹ፣ለእናንተ ወዮላችሁ የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትሻላችሁ?ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።

19. ይህ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሲሸሽ፣ድብ እንደሚያጋጥመው፣ወደ ቤቱም ገብቶ፣ እጁን በግድግዳውላይ ሲያሳርፍ፣እባብ እንደሚነድፈው ነው።

20. የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ፣የብርሃን ጸዳል የሌለው ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?

21. “ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤ጠልቼውማለሁ፤ ጉባኤዎቻችሁ ደስ አያሰኙኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አሞጽ 5