ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 5:12-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ኀጢአታችሁ ምንኛ ታላቅ እንደሆነ፣በደላችሁም የቱን ያህል እንደ በዛ እኔ ዐውቃለሁና።ጻድቁን ትጨቊናላችሁ፤ጒቦም ትቀበላላችሁ፤በፍርድ አደባባይም ከድኻው ፍትሕ ትነጥቃላችሁ።

13. ስለዚህ አስተዋይ ሰው በእንዲህ ያለ ጊዜ ዝም ይላል፤ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና።

14. በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፣መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ከዚያ በኋላ እንደ ተናገራችሁት፣የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።

15. ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ፤በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ፤ምናልባትም የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር፣ለዮሴፍ ትሩፍ ይራራ ይሆናል።

16. ስለዚህ ጌታ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በየመንገዱ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤በአደባባዩም የሥቃይ ጩኸት ይሆናል፤ ገበሬዎች ለልቅሶ፣አልቃሾችም ለዋይታ ይጠራሉ።

17. በየወይኑ ዕርሻ ሁሉ ወየው ተብሎ ይለቀሳል፤እኔ በመካከላችሁ አልፋለሁና፤”ይላል እግዚአብሔር።

18. የእግዚአብሔርን ቀን ለምትሹ፣ለእናንተ ወዮላችሁ የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትሻላችሁ?ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።

19. ይህ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሲሸሽ፣ድብ እንደሚያጋጥመው፣ወደ ቤቱም ገብቶ፣ እጁን በግድግዳውላይ ሲያሳርፍ፣እባብ እንደሚነድፈው ነው።

20. የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ፣የብርሃን ጸዳል የሌለው ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?

21. “ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤ጠልቼውማለሁ፤ ጉባኤዎቻችሁ ደስ አያሰኙኝም።

22. የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ብታቀርቡልኝም፣እኔ አልቀበለውም፤ከሰቡ እንስሶቻችሁ የኅብረት መሥዋዕት ብታቀርቡልኝም፣እኔ አልመለከተውም።

23. የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤የበገናህንም ዜማ አልሰማም።

24. ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።

25. “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣መሥዋዕትንና ቊርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን?

26. ለራሳችሁ የሠራችሁትን፣የንጉሣችሁን ቤተ ጣዖት፣የጣዖቶቻችሁን ዐምድ፣የአምላካችሁን ኮከብ አንሥታችሁ ተሸከማችሁ።

27. ስለዚህ ከደማስቆ ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋችኋለሁ፤”ይላል ስሙ የሰራዊት አምላክ የሆነ እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አሞጽ 5