ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 24:7-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. አዲሱ የወይን ጠጅ አለቀ፤ የወይኑም ተክል ደረቀ፤ደስተኞችም ሁሉ አቃሰቱ።

8. የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ደስ የሚያሰኘውም በገና እረጭ አለ።

9. ከእንግዲህ እየዘፈኑ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤መጠጡም ለሚጠጡት ይመራል።

10. የፈራረሰችው ከተማ ባድማ ሆነች፤የየቤቱም መግቢያ ተዘጋ።

11. በየአደባባዩ የወይን ጠጅ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ፤ደስታው ሁሉ ወደ ሐዘን ይለወጣል፤ሐሤቱም ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍቶአል።

12. ከተማዪቱ ፈጽማ ፈርሳለች፤በሮቿም ደቀው ወድቀዋል።

13. የወይራ ዛፍ ሲመታ፣የወይንም ዘለላ ሲቈረጥ ቃርሚያ እንደሚቀር ሁሉ፣በምድሪቱ ላይ፣በሕዝቦችም ላይ እንዲሁ ይሆናል።

14. ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤ በደስታም ይጮኻሉ፤ከምዕራብም የእግዚአብሔርን ክብር ያስተጋባሉ።

15. ስለዚህ በምሥራቅ ለእግዚአብሔር ክብር ስጡ፤ከባሕር ደሴቶችም፣የእስራኤልን አምላክ፣ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ አድርጉ።

16. “ለጻድቁ ክብር ይሁን” የሚል ዝማሬ፣ከምድር ዳርቻ ሰማን፤እኔ ግን፣ “ከሳሁ፤ መነመንሁ፤ወዮልኝ!ከዳተኞች አሳልፈው ሰጡ፤ከዳተኞች በክሕደታቸው አሳልፈው ሰጡ” አልሁ።

17. በምድር የምትኖር ሕዝብ ሆይ፤ሽብር፣ ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቁሃል።

18. ከሽብር ድምፅ የሚሸሽ፣ወደ ጒድጓድ ይገባል፤ከጒድጓድ የወጣም፣በወጥመድ ይያዛል።የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፤የምድርም መሠረት ተናወጠ።

19. ምድር ተከፈለች፤ምድር ተሰነጠቀች፤ምድር ፈጽማ ተናወጠች።

20. ምድር እንደ ሰካራም ዞረባት፤ነፋስ እንደሚወዘውዘውም ጐጆ ሆነች፣የዐመጿ ሸክም ከባድ ስለ ሆነ ትወድቃለች፤እንደ ገናም አትነሣም።

21. በዚያ ቀን እግዚአብሔር፣በላይ በሰማያት ያሉትን ኀይሎች፣በታችም በምድር ያሉትን ነገሥታት ይቀጣቸዋል።

22. በጒድጓድ ውስጥ እንዳሉ እስረኞች፣በአንድ ላይ ይታጐራሉ፤በእስር ቤት ይዘጋባቸዋል፣ከብዙ ቀንም በኋላ ለፍርድ ይቀርባሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 24