ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 45:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ለቀባሁት፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት፣ነገሥታትን ትጥቅ አስፈታ ዘንድ፣ሕዝብን ሁሉ ላስገዛለት፣ደጆች እንዳይዘጉ፣በሮቹን በፊቱ ለምከፍትለት፣ለቂሮስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

2. ‘በፊትህ እሄዳለሁ፤ተራሮችን እደለድላለሁ፤የናስ በሮችን እሰብራለሁ፤የብረት መወርወሪያዎችንም እቈርጣለሁ።

3. በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።

4. ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ስለ መረጥሁት ስለ እስራኤል፣አንተ ባታውቀኝ እንኳ፣በስምህ ጠርቼሃለሁ፤የክብርም ስም ሰጥቼሃለሁ።

5. እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤ከእኔ በቀር አምላክ የለም።አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣እኔ አበረታሃለሁ።

6. ይኸውም ሰዎች ከፀሓይ መውጫ፣እስከ መጥለቂያው፣ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው፤እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም።

7. እኔ ብርሃንን ሠራሁ፤ ጨለማንም ፈጠርሁ፤አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’

8. “እናንት ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤ምድር ትከፈት፤ድነት ይብቀል፤ጽድቅም አብሮት ይደግ፤እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።

9. “ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ከሠሪው ጋር ክርክር ለሚገጥም ወዮለት፤ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን?የምትሠራውስ ሥራ፣‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?

10. አባቱን፣‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣እናቱንም፣‘ምን ወለድሽ’? ለሚል ወዮለት።

11. “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን?ስለ እጆቼስ ሥራ ታዙኛላችሁን?

12. ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 45