ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 45:9-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. “ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ከሠሪው ጋር ክርክር ለሚገጥም ወዮለት፤ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን?የምትሠራውስ ሥራ፣‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?

10. አባቱን፣‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣እናቱንም፣‘ምን ወለድሽ’? ለሚል ወዮለት።

11. “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን?ስለ እጆቼስ ሥራ ታዙኛላችሁን?

12. ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።

13. ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ነጻ ያወጣል፤’ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”

14. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የግብፅ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣ወደ አንተ ይመጣሉ፤የአንተ ይሆናሉ፤ከኋላ ይከተሉሃል፤በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣በፊትህ እየሰገዱ፣‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”

15. አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።

16. ጣዖት ሠሪዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀላሉ፤በአንድነት ይዋረዳሉ።

17. እስራኤል ግን በእግዚአብሔር፣በዘላለም ድነት ይድናል፤እናንተም ለዘላለም፣አታፍሩም፤ አትዋረዱም።

18. ሰማያትን የፈጠረ፣እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣የመሠረታት፣የሰው መኖሪያ እንጂ፣ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ከእኔም በቀር ሌላ የለም።

19. በጨለማ ምድር፣በምስጢር አልተናገርሁም፤ለያዕቆብም ዘር፣“በከንቱ ፈልጉኝ” አላልሁም።እኔ እግዚአብሔር እውነትን እናገራለሁ፤ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለው።’

20. “በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤እናንት ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ።የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 45