ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 46:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ።ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ።

5. “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋር እኩል ታደርጉኛላችሁ?እንመሳሰልስ ዘንድ ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ?

6. ሰዎች ወርቅ ከከረጢታቸው ይዘረግፋሉ፤ብርንም በሚዛን ይመዝናሉ፤አንጥረኛን ይቀጥራሉ፤ እርሱም አምላክ አድርጎ ያበጅላቸዋል።እነርሱም ይሰግዱለታል፤ ያመልኩታልም።

7. አንሥተው በትከሻቸው ይሸከሙታል፤እቦታው ያደርጉታል፤ በዚያም ይቆማል፤ከዚያም ቦታ አይንቀሳቀስም፤ማንም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይመልስም፤ከጭንቅቱም አያድነውም።

8. “እናንት በደለኞች፣ ይህን አስታውሱ፤አስቡበትም፤ በልባችሁም ያዙት።

9. የጥንቱን፣ የቀደመውን ነገር አስታውሱ፤እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም።

10. የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ፤‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።

11. ከምሥራቅ ነጣቂ አሞራ፣ከሩቅ ምድር ዐላማዬን የሚፈጽም ሰው እጠራለሁ።የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤ያቀድሁትን እፈጽማለሁ።

12. እናንት እልኸኞች፣ከጽድቅም የራቃችሁ ስሙኝ።

13. ጽድቄን እያመጣሁ ነው፤ሩቅም አይደለም፤ማዳኔም አይዘገይም።ለጽዮን ድነትን፣ለእስራኤል ክብሬን አጐናጽፋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 46