ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 14:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል የየነገዱ ጐሣ አባቶች የደለደሉላቸው፣ እስራኤላውያንም በከነዓን ምድር የወረሱት ርስት ይህ ነው።

2. ርስታቸውም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዕጣ ተከፋፈለ።

3. ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን አብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤

4. የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን አብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም፤

5. ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።

6. የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የአምላክ ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ።

7. የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤

8. አብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት።

9. ስለዚህም ሙሴ በዚያች ዕለት፣ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ተከትለኸዋልና እግርህ የረገጣት ምድር ለዘላለም የአንተና የዘርህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለልኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 14