ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 2:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ ምድሪቱን፣ በተለይም የኢያሪኮን ከተማ ሰልሉ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ፤ ሰዎቹም ሄደው ረዓብ ከተባለች ጋለ ሞታ ቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ።

2. ለኢያሪኮም ንጉሥ፣ “እነሆ፤ ምድሪቱን ሊሰልሉ ጥቂት እስራኤላውያን በሌሊት ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው።

3. የኢያሪኮም ንጉሥ፣ “ወደ አንቺ መጥተው ወደ ቤትሽ የገቡት ሰዎች ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ስለ ሆነ፣ እንድታስወጪአቸው” የሚል መልእክት ወደ ረዓብ ላከ።

4. ሴቲቱ ግን ሁለቱን ሰዎች ተቀብላ ሸሽጋቸው ስለ ነበር፣ እንዲህ አለች፤ “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም።

5. ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።”

6. ነገር ግን ሰዎቹን ጣራ ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር።

7. ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሄዱ፣ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደሄዱም የቅጥሩ በር ተዘጋ።

8. ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ ጣራው ወጥታ፣

9. እንዲህ አለቻቸው፤ “እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደሰጣችሁ፣ እናንተንም መፍራት እንዳደረብን፣ የዚህች አገር ነዋሪዎች ሁሉ ልባቸው በፊታችሁ መቅለጡንም ዐውቃለሁ።

10. ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል።

11. ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 2