ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 22:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. የዛራ ልጅ አካን፣ እርም የሆነውን ነገር በመውሰድ ኀጢአት ስለ ሠራ፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ላይ ቍጣ አልመጣምን? በሠራው ኀጢአት የሞተውም እርሱ ብቻ አልነበረም።”

21. ከዚያም የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል ጐሣ መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤

22. “ኀያሉ አምላክ፣ እግዚአብሔር! ኀያሉ አምላክ፤ እግዚአብሔር! እርሱ ያውቃል! እስራኤልም ይህን ይወቅ! ይህ የተደረገው በማመፅ ወይም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ከሆነ፣ ዛሬ አትማሩን!

23. መሠዊያውን የሠራነው እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ ለማለት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ልናሳርግበት ወይም የኅብረት መሥዋዕት ልናቀርብበት አስበን ከሆነ፣ ራሱ እግዚአብሔር ይበቀለን።

24. “እኛማ ይህን ያደረግነው፣ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ለዘሮቻችን እንዲህ እንዳይሏቸው ፈርተን ነው፤ “ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ?

25. እናንት የሮቤልና የጋድ ልጆች፤ እግዚአብሔር ዮርዳኖስን በመካከላችን መለያ ድንበር ስላደረገው፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም።’ ስለዚህ ዘሮቻችሁ፣ የእኛ ዘር እግዚአብሔርን እንዳይፈራ ሊያደርጉ ይችላሉ።

26. “እኛም ‘እንነሣና መሠዊያ እንሥራ፤ የምንሠራው መሠዊያ ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይውልም’ ያልነው ለዚህ ነው።

27. በሌላም በኩል የሚቃጠል መሥዋዕታችንን፣ ሌላውን ቊርባናችንንና የኅብረት መሥዋዕታችንን ይዘን በተቀደሰው ስፍራ እግዚአብሔርን እንደምናመልክ መሠዊያው በእኛና በእናንተ እንዲሁም በሚቀጥሉት ትውልዶች መካከል ምስክር ይሆናል። ስለዚህ ወደ ፊት ዘሮቻችሁ ዘሮቻችንን፣ ‘ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም’ ሊሏቸው አይችሉም።

28. “እኛም፣ ‘ወደ ፊት እኛንም ሆነ ዘሮቻችንን እንዲህ የሚሉ ከሆነ፣ “እነሆ፤ አባቶቻችን የሠሩትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ ተመልከቱ፤ ይህ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር እንዲሆን እንጂ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ አይደለም ብለን እንመልሳለን’ ” አልን።

29. “በማደሪያው ድንኳን ፊት ካለው ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለእህል ቊርባን እንዲሁም ለሌላ መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በመሥራት ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ እናምፅን? እርሱን ማምለካችንንም እንተውን? ይህ ከእኛ ይራቅ!”

30. ካህኑ ፊንሐስና የእስራኤላውያን የጐሣ መሪዎች የነበሩት የማኅበረ ሰቡ አለቆች የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ወገኖች ያሉትን በሰሙ ጊዜ ተደሰቱ።

31. የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም፣ የሮቤልን የጋድንና የምናሴን ወገኖች “በዚህ ነገር እግዚአብሔርን አልበደላችሁምና፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ዛሬ ዐውቀናል፤ እነሆ እስራኤላውያንን ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 22