ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 10:7-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እኔ በደለኛ እንዳልሆንሁ፣ከእጅህም ሊያስጥለኝ ማንም እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።

8. “እጅህ አበጀችኝ፤ ሠራችኝም፤መልሰህ ደግሞ ታጠፋኛለህን?

9. እንደ ሸክላ እንዳበጀኸኝ አስብ፤አሁን ደግሞ ወደ ትቢያ ትመልሰኛለህን?

10. እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን?እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን?

11. ቈዳና ሥጋ አለበስኸኝ፤በዐጥንትና በጅማትም አገጣጥመህ ሠራኸኝ።

12. ሕይወትን ሰጠኸኝ፤ በጎነትንም አሳየኸኝ፤እንክብካቤህም መንፈሴን ጠበቀ።

13. “ይህን ሁሉ ግን በልብህ ሸሸግህ፣ነገሩ በሐሳብህ እንደ ነበር ዐውቃለሁ፤

14. ኀጢአትን ብሠራ ትመለከተኛለህ፤መተላለፌንም ሳትቀጣ አታልፍም።

15. በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ንጹሕ ብሆንም፣ ራሴን ቀና አላደርግም፤ውርደትን ተከናንቤአለሁና፤በመከራም ተዘፍቄአለሁ፤

16. ራሴን ከፍ ከፍ ባደርግ፣ እንደ አንበሳ ታደባብኛለህ፤አስፈሪ ኀይልህን ደጋግመህ ታሳየኛለህ፤

17. አዳዲስ ምስክሮችን ታመጣብኛለህ፤ቍጣህንም በላዬ ትጨምራለህ፤ሰራዊትህም ተከታትሎ ይመጣብኛል።

18. “ታዲያ ለምን ከማሕፀን አወጣኸኝ?ምነው ዐይን ሳያየኝ በሞትሁ ኖሮ!

19. ምነው ባልተፈጠርሁ!ወይም ከማሕፀን ቀጥታ ወደ መቃብር በወረድሁ!

20. ጥቂት የሆነው ዘመኔ እያለቀ አይደለምን?ከሥቃዬ ፋታ እንዳገኝ ተወት አድርገኝ፤

21. ወደማልመለስበት ስፍራ፣ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ አገር ከመሄዴ በፊት፣

22. ብርሃኑ እንደ ጨለማ ወደ ሆነበት፣የሞት ጥላ ወዳረበበበት፣ ሥርዐት የለሽ ወደ ሆነ ምድር፣ድቅድቅ ጨለማ ወደ ሰፈነበት አገር ሳልሄድ ተወኝ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 10