ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 34:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኤሊሁ በመቀጠል እንዲህ አለ፤

2. “እናንት ጠቢባን፣ ቃሌን ስሙ፤ዐዋቂዎችም አድምጡኝ።

3. ምላስ ምግብን አጣጥሞ እንደሚለይ፣ጆሮም የንግግርን ለዛ ለይቶ ያውቃል።

4. የሚበጀንን እንምረጥ፣መልካሙንም አብረን እንወቅ።

5. “ኢዮብ እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤እግዚአብሔር ግን ፍትሕ ነሣኝ፤

6. እውነተኛ ብሆንም፣እንደ ውሸታም ተቈጥሬአለሁ፤በደል ባይኖርብኝም፣በማይፈወስ ቍስል ተመትቻለሁ።’

7. ፌዝን እንደ ውሃ የሚጠጣት፣እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?

8. ከክፉ አድራጊዎች ጋር ይተባበራል፤ከኀጢአተኞችም ጋር ግንባር ይፈጥራል።

9. ‘እግዚአብሔርን ለማስደሰት መሞከር፣ለሰው አንዳች አይጠቅምም’ ብሎአልና።

10. “ስለዚህ፣ እናንተ አስተዋዮች ስሙኝ፤ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ።

11. ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፤እንደ አካሄዱም ይከፍለዋል።

12. በእውነት እግዚአብሔር ክፋትን አይሠራም፤ሁሉን የሚችል አምላክ ፍትሕን አያጣምምም።

13. ምድርን እንዲገዛ የሾመው አለን?የዓለምስ ሁሉ ባለቤት ያደረገው ማን ነው?

14. እርሱ መንፈሱን መልሶ ቢወስድ፣እስትንፋሱንም ወደ ራሱ ቢሰበስብ፣

15. ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት በጠፋ፣ሰውም ወደ ዐፈር በተመለሰ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 34