ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 36:5-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “እግዚአብሔር ኀያል ነው፤ ግን ማንንም አይንቅም፤ኀያል፣ በዐላማውም ጽኑ ነው።

6. ክፉዎችን በሕይወት አያኖርም፤ለተቸገሩት ግን በቅን ይፈርዳል።

7. ዐይኖቹን ከጻድቃን ላይ አያነሣም፤ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፤ለዘላለምም ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።

8. ነገር ግን ሰዎች በሰንሰለት ቢታሰሩ፣በመከራም ገመድ ቢጠፈሩ፣

9. በእብሪት የፈጸሙትን በደል፣ተግባራቸውን ይነግራቸዋል።

10. ተግሣጽን እንዲሰሙ ያደርጋቸዋል፤ከክፋታቸውም እንዲመለሱ ያዛቸዋል።

11. ታዘው ቢያገለግሉት፣ቀሪ ዘመናቸውን በተድላ፣ዕድሜያቸውንም በርካታ ይፈጽማሉ።

12. ባይሰሙ ግን፣በሰይፍ ይጠፋሉ፤ያለ ዕውቀትም ይሞታሉ።

13. “ልባቸው ከእግዚአብሔር የራቀ፣ ቍጣን ያስተናግዳሉ፤በሰንሰለት ባሰራቸውም ጊዜ እንኳ ወደ እርሱ አይጮኹም።

14. በቤተ ጣዖት ውስጥ ዝሙት በሚፈጽሙት መካከል፣ገና በወጣትነታቸው ይቀጫሉ።

15. ነገር ግን የሚሠቃዩትን ከሥቃያቸው ያድናቸዋል፤በመከራቸውም ውስጥ ይናገራቸዋል።

16. “አንተንም ከመከራ መንጋጋ፣ጭንቀት ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ፣ምርጥ ምግብ ወደ ሞላበት ማእድ ያወጣሃል።

17. አሁን ግን ለክፉዎች የሚገባው ፍርድ በላይህ ተጭኖአል፤ፍርድና ብይን ይዘውሃል።

18. ባለጠግነት እንዳያታልልህ፣የእጅ መንሻ ብዛትም እንዳያስትህ ተጠንቀቅ።

19. ባለጠግነትህም ሆነ ብርቱ ጥረትህ ሁሉ፣ችግር ውስጥ እንዳትገባ ሊረዳህ ይችላልን?

20. ሰዎች ከቤታቸው የሚወሰዱበትን፣ሌሊት አትመኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 36