ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 10:12-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እግዚአብሔር ግን ምድርን በኀይሉ ፈጠረ፤ዓለምን በጥበቡ መሠረተ፤ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ።

13. ድምፁን ሲያንጐደጒድ፣ በሰማያት ያሉ ውሆች ይናወጣሉ፤ጉሙን ከምድር ዳር ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

14. እያንዳንዳቸው ጅሎችና ዕውቀት የለሾች ናቸው።ወርቅ አንጥረኛውም ሁሉ በሠራው ጣዖት ዐፍሮአል፤የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤እስትንፋስም የላቸውም።

15. እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።

16. የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደነዚህ አይደለም፤እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

17. አንቺ የተከበብሽ፤ከያለበት ንብረትሽን ሰብስቢ፤

18. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤“በዚህች ምድር የሚኖሩትን፣አሁን ወደ ውጪ እወነጭፋቸዋለሁ፤ጒዳቱ እንዲሰማቸው፣መከራ አመጣባቸዋለሁ፤”

19. ስለ ስብራቴ ወዮልኝ፤ቍስሌም የማይድን ነው፤ግን ለራሴ እንዲህ አልሁት፤“ይህ የኔው ሕመም ነው ልሸከመውም ይገባኛል።”

20. ድንኳኔ ፈርሶአል፤ገመዶቹም ሁሉ ተበጣጥሰዋል፤ልጆቼ ጥለውኝ ሄደዋል፤ ከእንግዲህም አይመለሱም፤ድንኳኔን ለመትከል፣መጋረጃዬንም ለመዘርጋት ማንም የቀረ የለም።

21. እረኞቹ አእምሮ የላቸውም፤ እግዚአብሔርን አይጠይቁም፤ስለዚህ አልተከናወነላቸውም፤መንጎቻቸውም ሁሉ ተበታትነዋል።

22. መርዶ ስሙ! እነሆ፤ ከሰሜን ምድር፣ታላቅ ሽብር እየመጣ ነው፤የይሁዳን ከተሞች ባድማ፣የቀበሮዎችም መናኸሪያ ያደርጋል።

23. እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራእንደማይችል ዐውቃለሁ።

24. እግዚአብሔር ሆይ፤ ቅጣኝ፤ ብቻ በመጠኑ ይሁንልኝ፤ፈጽሞ እንዳልጠፋ፣በቍጣህ አትምጣብኝ።

25. ያዕቆብን አሟጠው ስለበሉት፣ፈጽመው ስለዋጡት፣መኖሪያውንም ወና ስላደረጉ፣በማያውቁህ ሕዝቦች፣ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ፣ቍጣህን አፍስስ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 10