ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 2:9-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. “ስለዚህ እንደ ገና ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፤”“ከልጅ ልጆቻችሁም ጋር እከራከራለሁ።ይላል እግዚአብሔር።

10. ወደ ኪቲም ጠረፍ ተሻገሩና እዩ፤ወደ ቄዳርም ልካችሁ በጥንቃቄ መርምሩ፣እንዲህ ዐይነት ነገር ተደርጎ ያውቅ እንደሆነ ተመልከቱ፤

11. የእውነት አማልክት ባይሆኑም እንኳ፣አማልክቱን የለወጠ ሕዝብ አለን?ሕዝቤ ግን ክብራቸውሠ የሆነውን፣በከንቱ ነገር ለወጡ።

12. ሰማያት ሆይ፤ በዚህ ተገረሙ፤በታላቅ ድንጋጤም ተንቀጥቀጡ፤”ይላል እግዚአብሔር።

13. “ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል፣ሕያው የውሃ ምንጭ የሆንሁትን፣እኔን ትተዋል፤ውሃ መያዝ የማይችሉትን ቀዳዳ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች፣ለራሳቸው ቈፍረዋል።

14. እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውልድ ባሪያ?ታዲያ፣ ስለ ምን ለብዝበዛ ተዳረገ?

15. አንበሶች በእርሱ ላይ አገሡ፤በኀይለኛ ድምፅም ጮኹበት።ምድሩን ባድማ አድርገውበታል፤ከተሞቹ ተቃጥለዋል፤ ወናም ሆነዋል።

16. ደግሞም የሜምፎስና የጣፍናስ ሰዎች፣መኻል ዐናትሽን ላጩሽ።

17. በመንገድ የሚመራሽን፣ እግዚአብሔር አምላክሽን በመተውሽ፣ይህን በራስሽ ላይ አላመጣሽምን?

18. ከሺሖር ወንዝ ውሃ ለመጠጣት፣አሁንስ ለምን ወደ ግብፅ ወረድሽ?ከኤፍራጥስ ወንዝስ ውሃ ለመጠጣት፣ወደ አሦር መውረድ ለምን አስፈለገሽ?

19. ክፋትሽ ቅጣት ያስከትልብሻል፤ክህደትሽም ተግሣጽ ያመጣብሻል፤ እግዚአብሔር አምላክሽን ስትተዪ፣እኔንም መፍራት ችላ ስትይ፣ምን ያህል ክፉና መራራ እንደሚሆንብሽ፣አስቢ፤ እስቲ አስተውዪ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

20. “ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰበርሁ፤እስራትሽን በጣጠስሁ፤አንቺም፣ ‘አላገለግልህም’ አልሽ፤ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ሥር፣በያንዳንዱም ለምለም ዛፍ ሥር፣ለማመንዘር ተጋደምሽ።

21. እኔ፣ እንደ ምርጥ የወይን ተክል፣ጤናማና አስተማማኝ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ታዲያ ብልሹ የዱር ወይን ተክል ሆነሽ፣እንዴት ተለወጥሽብኝ?

22. በልዩ ቅጠል ብትታጠቢ፣ብዙ ሳሙና ብትጠቀሚም፣የበደልሽ ዕድፍ አሁንም በፊቴ ነው፤”ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

23. “ ‘አልረከስሁም፣በኣሊምን አልተከተልሁም’ እንዴት ትያለሽ?በሸለቆ ውስጥ ምን እንዳደረግሽእስቲ አስቢ፣ምንስ እንደ ፈጸምሽ ተገንዘቢ፤እንደምትፋንን ፈጣን ግመል ሆነሻል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 2