ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 21:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በዚህች ከተማ የሚኖሩትን፣ ሰዎችንም ሆኑ እንስሳትን እመታለሁ፤ እነርሱም በታላቅ መቅሠፍት ይሞታሉ።

7. ከዚያ በኋላ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን፣ ከመቅሠፍት፣ ከሰይፍና ከራብ የተረፈውንም ሕዝብ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆርና ሕይወታቸውን ለማጥፋት ለሚሹ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፤ አይራራላቸውም፤ አይምራቸውምም።’

8. “በተጨማሪም ለዚህ ሕዝብ እንዲህ በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እነሆ፤ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤

9. በዚህች ከተማ የሚቈይ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት ይሞታል፤ ወጥቶ ለከበቧችሁ ባቢሎናውያን እጁን የሚሰጥ ግን ነፍሱን ያተርፋል፤ በሕይወትም ይኖራል።

10. በዚህች ከተማ ላይ በጎ ሳይሆን ክፉ ለማድረግ ወስኛለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ለባቢሎን ንጉሥ ትሰጣለች፤ እርሱም በእሳት ያጠፋታል።’

11. “ለይሁዳ ንጉሥ ቤትም እንዲህ በል፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

12. የዳዊት ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ካደረጋችሁት ክፋት የተነሣ፣ቍጣዬ እንዳይቀጣጠል፣ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል እንዳይነድ፣በየማለዳው ፍትሕን አድርጉ፤የተበዘበዘውን ሰው፣ከጨቋኙ እጅ አድኑት።

13. ከሸለቆው በላይ፣በድንጋያማው ዐምባ ላይ የምትኖሪ ሆይ፤እኔ በአንቺ ላይ ወጥቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።“ማን በእኛ ላይ ይወጣል?ማንስ ወደ መኖሪያችን ደፍሮ ይገባል?” የምትሉ ሆይ፤

14. እንደ ሥራችሁ መጠን እቀጣችኋለሁ፤ይላል እግዚአብሔር፤በዱሯም እሳት እለኵሳለሁ፤በዙሪያዋ ያለውንም ሁሉ ይበላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 21