ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 38:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለባቢሎን ንጉሥ የጦር መኰንኖች እጅህን ብትሰጥ፣ ሕይወትህ ትተርፋለች፤ ይህችም ከተማ አትቃጠልም፤ አንተና ቤተ ሰብህም በሕይወት ትኖራላችሁ።

18. ለባቢሎን ንጉሥ የጦር መኰንኖች እጅህን ባትሰጥ ግን ይህች ከተማ ለባቢሎናውያን ዐልፋ ትሰጣለች፤ እነርሱም ያቃጥሏታል፤ አንተም ራስህ ከእጃቸው አታመልጥም።’ ”

19. ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፣ “ወደ ባቢሎን የኰበለሉት አይሁድ እንዲያላግጡብኝ፣ ባቢሎናውያን ለእነርሱ ዐሳልፈው ይሰጡኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው።

20. ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “ዐሳልፈው አይሰጡህም፣ ብቻ የምነግርህን የእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፤ መልካም ይሆንልሃል፤ ሕይወትህም ትተርፋለች።

21. እጅህን ለመስጠት እንቢ ብትል ግን፣ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ነገር ይህ ነው፤

22. በይሁዳ ቤተ መንግሥት የቀሩ ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎናውያን ባለ ሥልጣኖች ይወሰዳሉ፤ ሴቶቹም እንዲህ ይላሉ፤“ ‘እነዚያ የተማመንህባቸው ወዳጆችህ፣አሳሳቱህ፤ አሸነፉህ።እግርህ ጭቃ ውስጥ ተሰንቅሮአል፣ወዳጆችህ ጥለውህ ሄደዋል።’

23. “ሚስቶችህና ልጆችህ ሁሉ ተወስደው ለባቢሎናውያን ይሰጣሉ፤ አንተም ራስህ በባቢሎን ንጉሥ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።”

24. ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፤ “ስለዚህ ስለ ተነጋገርነው ነገር ማንም አይወቅ፤ አለዚያ ትሞታለህ።

25. መኳንንቱ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ሰምተው ወደ አንተ ቢመጡና፣ ‘ንጉሡን ምን እንዳልኸው፣ ንጉሡም ምን እንዳለህ ንገረን፤ ሳትደብቅ ንገረን፤ አለዚያ እንገድልሃለን’ ቢሉህ፣

26. ‘በዚያ እንዳልሞት ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ ንጉሡን ስለ ምን ነበር’ በላቸው።”

27. መኳንንቱ ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፤ እርሱም ንጉሡ ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ ከንጉሡ ጋር የተነጋገሩትን ነገር የሰማ አንድም ሰው ስላልነበረ፣ ከዚህ በላይ አላነጋገሩትም።

28. ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ ኤርምያስ በዘበኞች አደባባይ ተቀመጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 38